ባገባደድነዉ የትምህርት ዘመን የተፋጠነ ትምህርት ሲሰጥ ከነበሩበት 5 ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነዉና በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘዉ 03 ት/ቤት በዛሬዉ ዕለት ተማሪዎቹን አስመርቋል ።

የምረቃዉን ፕሮግራም በንግግር የከፈቱት የካፋ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ብርሃኑ እንደተናገሩት ከሆነ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም ጭምር ናቸዉ ብለዋል።

አቶ ይገዙ አክለዉም በዚህ ፕሮጀክት የታቀፉ እነዚህ ተማሪዎች ማንበብ መፃፍና መሠረታዊ የሂሳብ ስሌትን ማወቅ መቻላቸዉን የተናገሩ ሲሆን፤ የ 03 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርንና የመምህራን ስታፎችን ላደረጉት በጎ ተፅዕኖ አመስግነዋል ።

የዚህ ፕሮግራም የ03 ትምህርት ቤት ሱፐርቫይዘር ወ/ሮ ሄለን ሳህሌ በበኩላቸው፤ የጄኔቫ ግሎባል አጠቃላይ አላማን በማስተዋወቅ ንግግራቸዉን የጀመሩ ሲሆን የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም በዞናችን ተደራሽ የሆኑ ቦታዎችንና ተጠቃሚ ያደረጋቸዉን ተማሪዎች ቁጥር በመጥቀስ አብራርተዋል።

በዚህ ፕሮጀክት በዞን በወረዳ እና በቦንጋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላለፉት 10 ወራቶች ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ መሆናቸዉን የገለፁት ወ/ሮ ሄለን ፕሮግራሙ 472 የሚደርሱ የሕብረተሰቡን ክፍሎች በቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በዚህ ዝግጅት ላይ የካፋ ዞን የትምህርት መምሪያ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጀማል አባመጫ በበኩላቸዉ፤ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናችን ዕድለኝነት መሆኑን ገልፀዉ፤ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር እና ባለድርሻ አካላት በማመስገን ለተማሪዎችና ለተማሪ ወላጆች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የተማሪ ወላጆች እና ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት በታደሙበት በዚህ የመዝግያ ዝግጅት ላይ ፤ ተማሪዎች የተለያዩ መዝሙሮችና ግጥሞችን ያቀረቡ ሲሆን የተሻለ ዉጤት ላስመዝገቡ ተማሪዎች ሽልማት በማበርከት ዝግጅቱ ተጠናቋል።