በያዝነዉ አመት መጀመሪያ ላይ የካፋ ልማት ማህበር ጄኔቫ ግሎባል ከሚባል አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ተቋም ጋር በጥምረት እየሰራ የነበረዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ጥቂት የማይባሉ ዓላማዎች አንግቦ 2015 ዓ/ም የትምህርት ዘመን መቋጫ ላይ ደርሷል ።

መደበኛ የትምህርት እድልን በኢኮኖሚም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ያላገኙ’ና ፤ እድሜያቸው ከ ‘9’ እስከ ’14’ ዓመት የሆናቸው ህፃናት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መርሃ ግብርን ማቀላጠፍ ደግሞ ዋነኛዉና የመጀመሪያዉ የካፋ ልማት ማህበር እና የጄኔቫ ግሎባል አላማ ሆን ስራዉ ተከዉኗል።

በ2015 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በካፋ ዞን የጀመረዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም በአምስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለ180 ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን ፤ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 153 ተማሪዎች የተገባደደዉን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀዋል ።

በክልላችን ደረጃ የመጀመሪያዉ የሆነዉና በሁለት ወረዳዎች እንዲሁም በ 5 ትምህርት ቤቶች ይሰጥ የነበረዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም፤ በ2016 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ተደራሽነቱን ከፍ ለማድረግ ማቀዱ ተገልጿል ።

በዚህም መሠረት የተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም የሚሰጡበት ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 10 ከፍ እንደሚልና ከ 360 ተማሪዎች በላይ ደግሞ ተመዝግበዉ የዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።