በካፋ ልማት ማህበርና በጄኔቫ ግሎባል እየተሰጠ የሚገኘዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም

የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ማለት ዜጎች በሁሉም ቦታ’ና ሁኔታ የሚማሩበት እና ለትምህርት ጥሩ እሳቤ ያለው የሚማር ማህበረሰብ የመፍጠር ጉዳይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የካፋ ልማት ማህበር ጄኔቫ ግሎባል ከሚባል አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ተቋም ጋር በጥምረት እየሰራ የሚገኘዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት አንፃር ሁለት ጥቅሞች አሉት።

ዋነኛዉና የመጀመሪያዉ መደበኛ የትምህርት እድልን በኢኮኖሚም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ያላገኙ’ና ፤ እድሜያቸው ከ ‘9’ እስከ ’14’ ዓመት የሆናቸው ህፃናት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም ሲሆን ፤

በሁለተኛነት ደግሞ የተማሪዎቹን እናት አማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ በማሰብ በኢኮኖሚ ራሳቸዉን እንዲችሉ ማድረግ ነዉ።

ካፋ ላይ የትና እንዴት ይሰጣል ?

በካፋ ልማት ማህበርና በጄኔቫ ግሎባል አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚሰጠዉ ይህ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎች በሳምንት 6 ቀን እንዲሁም በቀን ለ 8 ሰዓታት የሚማሩበት የትምህርት ፕሮግራም ነዉ።

በ 2015 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በካፋ ዞን የጀመረዉ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም በክልላችን ደረጃ የመጀመሪያዉ ሲሆን፤ በሁለት ወረዳዎች በአምስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለ180 ተማሪዎች እየተሰጠ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል ቦንጋ ከተማ ዉስጥ የሚገኙ የዜሮ ሶስት እና የባንዲራ ትምህርት ቤቶች ዋነኛ ተጠቃሾች ሲሆኑ ፤ በጎባ ወረዳ አርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ቀሪ ሶስት ትምህርት ቤቶች ማለትም ዪሊዮ፣ አዲስፋና እና ኡዳሸከራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።

በአጠቃላይ፤ የተፋጠነ ትምህርት በሚሰጥበት ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 24 መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ፤ ወንበር፣ ሰሌዳ እና የሁሉም ተማሪዎችን የመማሪያ ቁሳ ቁሶችን በማሟላት ለዚህ የትምህርት ፕሮግራም መቀላጠፍ የካፋ ልማት ማህበር ድርሻ ከፍተኛ ነዉ።